Job 18

በልዳዶስ

1ሹሐዊው በልዳዶስ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2“ይህን ንግግር የምትጨርሰው መቼ ነው?
እስኪ ልብ ግዛ፤ ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን።
3ለምን እንደ ከብት መንጋ እንቈጠራለን?
እንደ ደንቈሮስ ለምን ታየናለህ?
4አንተ በቍጣ የነደድህ እንደ ሆነ፣
ምድር ባዶዋን ትቀራለች?
ወይስ ዐለት ከስፍራው ተነቅሎ ይወሰዳል?

5“የክፉዎች መብራት ይጠፋል፤
የእሳቱም ነበልባል ድርግም ይላል።
6የድንኳኑ ብርሃን ይጨልማል፤
መብራቱም በላዩ ይጠፋል፤
7የርምጃው ብርታት ይደክማል፤
የገዛ ዕቅዱም ይጥለዋል።
8እግሩ በወጥመድ ይያዛል፤
በመረብም ይተበተባል።
9አሽክላ ተረከዙን ይይዘዋል፤
ወስፈንጥርም ያጣብቀዋል።
10በምድር ላይ የሸንበቆ ገመድ፣
በመንገዱም ላይ ወጥመድ በስውር ይቀመጥለታል።
11ድንጋጤ በዙሪያው ያስፈራራዋል፤
ተከትሎም ያሳድደዋል።
12መቅሠፍት ሊውጠው ቀርቧል፤
ጥፋትም የእርሱን ውድቀት ይጠባበቃል።
13ደዌ ቈዳውን ይበላል፤
የሞት በኵርም ቅልጥሙን ይውጣል።
14ተማምኖ ከሚኖርበት ድንኳን ይነቀላል፤
ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ይነዳል።
15ድንኳኑ በእሳት ይያያዛል፤
ወይም ምንም አይተርፍለትም ማለት ነው።

በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል።
16ሥሩ ከታች ይደርቃል፤
ቅርንጫፉም ከላይ ይረግፋል።
17መታሰቢያው ከምድር ገጽ ይጠፋል፤
ስሙም በአገር አይነሣም።
18ከብርሃን ወደ ጨለማ ይጣላል፤
ከዓለምም ይወገዳል።
19በሕዝቡ መካከል ልጅ ወይም ዘር አይኖረውም፤
በኖረበትም አገር ተተኪ አያገኝም።
20ባጋጠመው ሁኔታ የምዕራብ ሰዎች ይደነግጣሉ፤
የምሥራቅም ሰዎች በፍርሀት ይዋጣሉ።
21በርግጥ የክፉ ሰው መኖሪያ፣
እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው መድረሻ ይህ ነው።”
Copyright information for AmhNASV